የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታሕሳስ 13, 2011 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

  1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በኢትዮጵያ ስፔስ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ ከሀገራዊ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት አቅጣጫ ጋር ተጣጥሞ ስፔስ በሂደት እንደ አንድ ንኡስ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሃገራችን ከዘርፉ ማግኘት ያለበታን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ አንድ ወጥ ፖሊሲ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስፔስ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ማስተካከያዎችን በማከል ፖሊሲው በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።
  2. ምክር ቤቱ ቀጥሎ የተወያየበት አጀንዳ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደ አገራዊ የዜና አገልግሎት የተረጋገጠ መረጃ ለመስጠት እና ተወዳዳሪ አቅም ለመገንባት የሚያስችለው ተቋማዊና የአሰራር ነጻነት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት አገልግሎቱ እንደገና ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
  3. የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከልን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ሌላው ለምክር ቤቱ የቀረበ አጀንዳ ነው፡፡ የህገ መንግስትና ፌደራሊዝም ስርአት አስተምህሮ ዜጎች በሕገ መንግስታዊነትና በፌደራሊዝም ላይ ያለቸውን ግንዛቤ ለማስፋት እና የመቻቻል ባህልን ለማጎልበት፤ አገራዊ እሴቶችን ለማዳበር ያላቸው ሚና የላቀ በመሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከልን ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
  4. በመጨረሻም ም/ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የዜጎችን ለሕጋዊ ዓላማ የመደራጀት መብት ለማረጋጋጥ እና በአገሪቱ ልማትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት ለማድረግ የተመቻቸ ምህዳር ለመፍጠር፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተጠያቂነት እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ማስተካከያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።